ከፌዴራል መንግሥት በጀት በሕግ በተቀመጡ መመዘኛዎች መሠረት ከተመደበው 20 ሚሊዮን ብር ውስጥ፣ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰባት ሚሊዮን ብር ሕግን በመጣስ ኢሕአዴግ ለመረጣቸው ፓርቲዎች አከፋፍሏል በሚል በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጥያቄ ቀረበበት፡፡
“ፓርቲዎች ከዜጎች ገንዘብ እየተቀበሉ የቪዛ የድጋፍ ደብዳቤ ሲሰጡ ቦርዱ ችላ ብሏል” አቶ ግርማ ሰይፉ
“ሆደ ሰፊ የሆንነው ዴሞክራሲ እንዲጎለብት በማሰብ ነው”
ፕሮፌሰር መርጋ በቃና
ከፌዴራል መንግሥት በጀት በሕግ በተቀመጡ መመዘኛዎች መሠረት ከተመደበው 20 ሚሊዮን ብር ውስጥ፣ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰባት ሚሊዮን ብር ሕግን በመጣስ ኢሕአዴግ ለመረጣቸው ፓርቲዎች አከፋፍሏል በሚል በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጥያቄ ቀረበበት፡፡
በምርጫ ለሚሳተፉ ፓርቲዎች ሥራ ማስፈጸሚያና ለዕለት ተዕለት ተግባራት ማከናወኛ በጀት የማከፋፈል ሥልጣን የተሰጠው የምርጫ ቦርድ አመራሮች ለቀረበላቸው የሕግ ጥሰት ጥያቄ ምላሽ ሳይሰጡ አልፈውታል፡፡ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ የሥራ አመራሮች የ2005 ዓ.ም. አጠቃላይ የሥራ አፈጻጸም ሪፖርታቸውን ባለፈው ሐሙስ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡበት ወቅት፣ በተጠቀሰው የሕግ ጥሰትና በሌሎች ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ እንዲሰጡ ተጠይቀዋል፡፡
የቦርዱ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መርጋ በቃና በዓመቱ ውስጥ የተካሄዱት የአዲስ አበባና የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤቶችና የአካባቢ ምርጫዎች ዴሞክራሲያዊና ነፃ ሆነው መጠናቀቃቸውን፣ ለዚህም ውጤት ቦርዱ ያከናወናቸውን ዝርዝር ተግባራት በ14 ገጽ ሪፖርታቸው ጨምቀው አቅርበዋል፡፡ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ወይም በክልል ምክር ቤቶች መቀመጫ ላላቸው አሥር የፖለቲካ ፓርቲዎች ለዕለት ከዕለት ተግባር ማከናወኛ በጀት 20 ሚሊዮን ብር ከመንግሥት በማስፈቀድ ባላቸው መቀመጫ ብዛት ተሰልቶ የባንክ ሒሳብ ቁጥራቸውን ላሳወቁ ስምንት የፖለቲካ ፓርቲዎች ማከፋፈሉን የቦርዱ ሪፖርት ያስረዳል፡፡ ይሁን እንጂ ከተጠቀሰው 20 ሚሊዮን ብር የትኛው ፓርቲ ምን ያህል እንዳገኘ አልተካተተም፡፡
ሪፖርቱ ከቀረበ በኋላ በምክር ቤቱ ብቸኛው የተቃዋሚ ፓርቲ ተወካይ የሆኑት አቶ ግርማ ሰይፉ ለፓርቲዎች የሚከፋፈል የመደበው 20 ሚሊዮን ብር በጀት ላይ ጠንከር ያለ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡
ከተጠቀሰው 20 ሚሊዮን ብር የትኛው ፓርቲ ምን ያህል ወሰደ የሚል ጥያቄ ማንሳት እንደማይፈልጉ፣ ምክንያቱ ደግሞ መመዘኛው በሕግ የተቀመጠና ቦርዱን የሚመለከት ባለመሆኑ እንደሆነ፣ ነገር ግን በመመዘኛው መሠረት ኢሕአዴግና አጋሮቹ አብዛኛውን እንደወሰዱት ግልጽ መሆኑን በመጠቆም ነበር አቶ ግርማ ወደ ጥያቄያቸው የገቡት፡፡
በመመዘኛው መሠረት ኢሕአዴግ ካገኘው ገንዘብ ውስጥ ሰባት ሚሊዮን ብር የሚሆነውን በራሱ ፍላጎት ለመረጣቸው ፓርቲዎች እንዲከፋፈልለት በመጠየቅ ለቦርዱ መመለሱንና ቦርዱም በኢሕአዴግ ለተጠቆሙት ፓርቲዎች ማከፋፈሉን አቶ ግርማ ገልጸዋል፡፡ ጥያቄያቸውም ያጠነጠነው በዚህ ላይ ነው፡፡
“የተጠቀሰው ሰባት ሚሊዮን ብር በሕግ መሠረት ለተፈለገው ዓላማ ነው ወይ የዋለው?” በሚል ጠንከር ያለ ድምፀት ጥያቄያቸውን ያነሱት አቶ ግርማ፣ “በመጀመሪያ ደረጃ በምክር ቤት ወንበር ለሌላቸው ፓርቲዎች የመንግሥትን ገንዘብ የማደል ሥልጣን ለኢሕአዴግ ማን ሰጠው?” በማለት አክለዋል፡፡ በመቀጠልም ገንዘቡን ኢሕአዴግ ሳይሆን ያደለው ምርጫ ቦርድ መሆኑ እንዳስገረማቸው፣ “ኢሕአዴግ እገሌ እገሌ ለሚባሉት ፓርቲዎች ስጡልኝ ብሎ በጠየቀው መሠረት ገንዘቡን ለተባሉት ፓርቲዎች ያደለው ምርጫ ቦርድ ነው፤” ብለዋል፡፡
ይህንኑ ጉዳይ በወቅቱ የቦርዱን ሰብሳቢ በአካል አግኝተዋቸው እንዴት ይህንን ታደርጋላችሁ የሚል ጥያቄ አንስተው እንደነበር ያስታወሱት አቶ ግርማ፣ ሰብሳቢው ፕሮፌሰር መርጋ በቃና በወቅቱ ምን ክፋት አለው የሚል ምላሽ እንደሰጧቸው በይፋ ተናግረዋል፡፡ “በእርግጥ በቅን ልቦና ስናስበው ምንም ክፋት የለውም፡፡ በሕግ ግን አይቻልም፡፡ በሕግ ላልተፈቀደላቸው ፓርቲዎች ምርጫ ቦርድ ገንዘብ ማደል አልተፈቀደለትም፤” በማለት፣ “በየትኛው ሥልጣናችሁ ገንዘቡን እንዳደላችሁ ያስረዱን፤” ሲሉ ፕሮፌሰር በቃናን በምክር ቤቱ ፊት ጠይቀዋል፡፡
ባነሱት የሕግ ጥሰት ጉዳይ ላይ የበለጠ ማስረዳት የመረጡት አቶ ግርማ፣ “በምሳሌ ላስረዳዎት፤ መንገዶች ባለሥልጣን የተፈቀደለትን በጀት መጨረስ ስላልቻለ ለጤና ጥበቃ ሚኒስቴር መስጠት አይችልም፤” ሲሉ የሕግ ጥሰቱን ለማሳየት ሞክረዋል፡፡
ከተጠቀሰው በመንግሥት ለፓርቲዎች የተፈቀደ 20 ሚሊዮን ብር በጀት ውስጥ ኢሕአዴግ በአከራካሪዎቹ መስፈርቶች ያገኘው ገንዘብ ግዙፍ ስለሆነበት ለሌሎች ፓርቲዎች እንዲከፋፈልለት ማድረግ እንደማይችል ገንዘቡን የማይፈልገው ከሆነ በሕግ አግባብ ማድረግ የሚችለው ለምርጫ ቦርድ መመለስ ብቻ ነው በማለት አስረድተዋል፡፡
“የእኔ ፓርቲ ከ20 ሚሊዮን ብር ውስጥ ለዓመት ሥራ ማስኬጃ የደረሰው ሦስት ሺሕ ብር ነው፡፡ እኛ ስለማይበቃን ገንዘቡን እንደመለስነው ኢሕአዴግም ይህንን ነበር ማድረግ ያለበት፤” ብለዋል፡፡ በማከልም ይህ ስህተት ሊታረም ይገባል ብለው፣ የሚታረመው ሌሎች ምክንያቶችን በመደርደር ሳይሆን ኢሕአዴግ ከሌላ የገንዘብ ምንጩ የተከፋፈለውን ገንዘብ ለምርጫ ቦርድ በመመለስ ብቻ ነው በማለት ተከራክረዋል፡፡
ከዚህ በተለየ ጉዳይ ጥያቄያቸውን ለምርጫ ቦርድ አመራሮች ማቅረባቸውን በመቀጠል፣ የመደራጀት መብት በአገሪቱ ስላለ ብቻ የፖለቲካ ፓርቲ እየመሠረቱ ነገር ግን ለፖለቲካ ተልዕኮ ሳይሆን ለሕገወጥ የገንዘብ መሰብሰቢያነት የሚጠቀሙ ፓርቲዎች መኖራቸው በግልጽ እየታወቀ፣ ቦርዱ ቸልተኝነትን መርጧል በማለት፣ “ሥራችሁ ምንድን ነው? ምንድን ነው የምታደርጉት?” ሲሉ አቶ ግርማ ጠይቀዋል፡፡ “በአሁኑ ወቅት ንግድ ፈቃድ ከማውጣት የፖለቲካ ፓርቲ ፈቃድ ማውጣት ይቀላል የተባለው እውነት እየሆነ ነው፡፡ ነገር ግን ንግድ ፈቃድ ያወጡ ግለሰቦች ፈቃዱን ካልተጠቀሙበት ይሰረዛሉ፤” የሚሉት አቶ ግርማ፣ “ፓርቲዎች ምን ሲያደርጉ ነው እዚህ አገር የሚሰረዙት?” በማለት ጥያቄ አቅርበዋል፡፡
ለዚህ ጥያቄያቸው ራሳቸው የሰጡት ምላሽ፣ የፖለቲካ ፓርቲ ፈቃድ ያላቸው ድርጅቶች ከፖለቲካ ዓላማ ይልቅ ከዜጎች ገንዘብ እየተቀበሉ የውጭ አገር የቪዛ ማስመቻ ድጋፍ ደብዳቤ በመጻፍ ዜጎችን ለስደት እየዳረጉ ነው የሚል ነው፡፡ “መንግሥት ለፓርቲዎች የሰጠውን የመንግሥት ቤት ለሌላ ሦስተኛ ወገን አከራይተው በጥቅም ሲጣሉ በሚዲያ እየተሰማ ቦርዱ ግን ዝምታን መርጧል፤” ሲሉ ተጨማሪ ወቀሳ ሰንዝረዋል፡፡
ለቀረቡት ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት የጀመሩት ፕሮፌሰር መርጋ በቃና፣ ለፓርቲዎች ተብሎ ከመንግሥት የሚመደበውን የድጎማ ገንዘብ ቦርዱ የሚያከፋፍለው ሕግን መሠረት አድርጎ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ በሕጉ መሠረትም ፓርቲዎቹ በፌዴራልም ሆነ በክልል ምክር ቤቶች ውስጥ ያላቸው መቀመጫ ብዛት አንደኛው መስፈርት መሆኑን፣ የሌሎቹ ፓርቲዎች ለቅስቀሳ ዘመቻ የሚያስፈልጋቸውን ወጪ በገንዘብና በዓይነት የሚሸፈን እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
በዚህ መስፈርት መሠረት ተጠቃሚ መሆን የሚገባቸው አሥር ፓርቲዎች እንደነበሩ፣ ከእነዚህ ውስጥ ለስምንቱ መከፋፈሉን ሁለቱ ግን የገንዘቡ መጠን ስላነሰባቸው አለመቀበላቸውን ገልጸው፣ “ገንዘቡን የወሰዱ ፓርቲዎች በምን ላይ እንዳዋሉት ኦዲት አስደርገው ማቅረብ አለባቸው፤” ብለዋል፡፡ ከዚህ ባለፈ ቦርዱ በኢሕአዴግ ጠቋሚነት በሕጉ መሠረት ለማይገባቸው ፓርቲዎች አከፋፍሏል ለሚለው ጥያቄ ምላሽ አልሰጡም፡፡
ፓርቲዎች ሕግን እንዲያከብሩ በተደጋጋሚ እየመከሩ መሆኑን የሚገልጹት ፕሮፌሰር መርጋ፣ “ሕጉ ሙሉ ለሙሉ ቢከበር ለቦርዱም ሥራ ቀለለለት ማለት ነው፡፡ ነገር ግን በሆደ ሰፊነት ነው የምንሠራው፡፡ ምክንያቱም ለዴሞክራሲና ለመድበለ ፓርቲ ሥርዓት መጎልበት ሲባል፤” ብለዋል፡፡
ቦርዱ በዚሁ ሁኔታ ይቀጥላል ማለት እንዳልሆነ የጠቆሙት ሰብሳቢው ሕግን ማክበር በማይችሉ ላይ ዕርምጃ ይወስዳል ብለዋል፡፡ “ለምሳሌ አራት ፓርቲዎች ፈቃድ ከወሰዱ በኋላ ከቦርዱ ጋር ግንኙነት በማቋረጣቸውና በተደጋጋሚ በሚዲያ ጥሪ ቢተላለፍላቸውም ባለመገኘታቸው ተሰርዘዋል፤” የሚሉት ፕሮፌሰር መርጋ፣ በአሁኑ ወቅት ፈቃድ ካላቸው 76 ፓርቲዎች ውስጥ 22 የሚሆኑት ሕጉን ሙሉ ለሙሉ ያሟሉ መሆናቸውን፣ የተቀሩት ግን በከፊል ማሟላታቸውንና ከእነዚህ ጋር በቀጣይ ሕግ የማስከበር ሥራን በመወያየት እንደሚያከናውኑ አብራርተዋል፡፡
source: Ethiopia Reporter
No comments:
Post a Comment