Saturday, July 13, 2013

መጪው ትውልድ ዕቁብ ገብቶ ይከፍለዋል

“ድሪምላይነር”
በዓለም ላይ የድሪምላይነር አውሮፕላን ባለቤቶች 10 አገራት ብቻ ሲሆኑ፤ ከአፍሪካ ብቸኛዋ፦”ዕዳን አትፍራው፤አንቆ አይገልህም”በሚል መርህ በብድር ከቦይንግ ካምፓኒ አውሮፕላኑን የገዛችው ኢትዮጵያ ብቻ ናት።
“መጪው ትውልድ ዕቁብ ገብቶ ይከፍለዋል” ብለን በብድር አንድ ድሪምላይነር መግዛታችንም -በድሪም ላይነር አውሮፕላን ከአፍሪካ 1ኛ ከ ዓለም 10ኛ አድርጎ አስቀመጠን። ይህም ኢትዮጵያ በቀንድ ከብት ብዛት ከአፍሪካ 1ኛ ከዓለም 10ኛ ተብለን በልጅነታችን የተማርነውን እንድናስታውስ አደረገንና ኮራ፣ቀብረር እንደማለት አደረገን።
ዳሩ ምን ያረጋል? ብድርንም፣አዲስ ቴክኖሎጅንም ደፍረን የገዛነው አውሮፕላን የሰው ዐይን በዝቶበት ይሁን አለያም የቤት ጣጣ አልለቅ ብሎት፦ ገና ከጅምሩ ማተኮስና መታመም አበዛ።
ድሪምላይነር አውሮፕላን ከወራት በፊት ተመሣሳይ ችግር አጋጥሞት በዓለማቀፍ ደረጃ ያሉት ድሪምላይነሮች በሙሉ በረራቸውን ማቆማቸውና አውሮፕላኑ ለዳግም ፍተሻ ወደ ቴክኒክ ምርመራ እንዲገባ መደረጉ ይታወሳል።አስገራሚው ነገር ምርመራው አልቋል ከተባለ በሁዋላ በ 10 አገሮች ውስጥ ካሉት ድሪምላይነሮች የመጀመሪያ በረራውን ያደረገው ትናንት ለንደን ላይ ችግር የተከሰተበት የኢትዮጵያ ድሪምላይነር መሆኑ ነበር-ከአዲስ አበባ-ናይሮቢ።ሌሎቹ አገሮች የኛን ሙከራ ካዩ በሁዋላ ነው የቀጠሉት።
በወቅቱ “ለምን ኢትዮጵያ ከጥገናው(ከቴክኒክ ምርመራው) በሁዋላ የመጀመሪያውን በረራውን አደረገች?”የሚል ጥያቄ ተፍጥሮብኝ ነበር።እኛ ጋር ሰው ረከስ ስለሚል ይሆን? ወይስ ዓለምን ያስጨበጨቡ ልዩ መካኒኮች ስላሉን? በእርግጥ ያን በረራ ቀድመን ስናደርግ አውሮፕላኑ ላይ ችግር ቢፈጠርም፤ ኢንሹራንስ እስካለው ድረስ የገንዘብ ኪሳራን በተመለከተ የሚደርስብን ነገር ላይኖር ይችላል። የሰው ህይወት ቢጠፋስ በምንድነው የሚካካሰው? የ አንድ ኢትዮጵያዊ ህይወት ዋጋው ስንት ነው?
እነሆ ይሄ የቤት ጣጣውን ያልጨረሰ ሸበላ ከጥቂት ጊዜ በሁዋላም ትናንት በለንደን-ሄትሮ አውሮፕላን ማረፊያ ላይ አተኩሶት ታምሞ(መለስተኛ ቃጠሎ ደርሶበት) ነበር። ልብን የ ያረጋጋው ዜና በቃጠሎው አንድም ሰው አለመጎዳቱ ነው። ይሁንና ቃጠሎው በአየር ላይ ሳለ እየበረረ ቢሆን ናሮ ሊፈጠር የሚችለው ነገር ሲታሰብ ይዘገንናል። …ለጥበቃው ፈጣሪን እናመሰግናለን። ለወደፊቱም- ጣጣውን ያልጨረሰ ቴክኖሎጅ መሞከሪያ ላለመሆን እንጠንቀቅ እንላለን!!

No comments:

Post a Comment