Thursday, July 18, 2013

በሳውዲ አረቢያ የኢትዮጵያው አምባሳደር መሃመድ ሐሰን በልታወቀ ምክንያት በአስቸኳይ ወደ ኢትዮጵያ ተጠሩ !

ሰሞኑንን በሳውዲ አረቢያ ሪያድ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን አምባሳደር መሃመድ ሃሰንን ጨምሮ አንዳንድ የኢትዮጵያ ዲፕሎማቶች በደል ፍጽመውብናል በሚል ታላቅ ተቃውሞ ከቦታቸው እንዲነሱ መጠየቃቸው ይታወሳል። በተለይ ጁላይ 7 2013 በሪያድ የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ አዳራሽ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር መ/ቤት የሴቶች እና የህጻናት ጉዳይ የመንግስት ተጠሪ ዶ/ር ደስታ ወ/ዮሃንስ በእንግድነት በተገኙበት በዚህ ስብሰባ አያሌ ወገኖች በአምባስደር ማህመድ ሃሰን እና ዲፕሎማቶቹ ላይ እንባ ቀረሽ ቅሬታ ማሰማታቸው ጉዳዩ በኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መ/ቤት ትኩረት ጊኝቶ መሰንበቱን ውስጥ አዋቂ ምንጮቻች ይገልጻሉ ፡፤

እነዚህ ውስጥ አዋቂ ምንጮች በሳውዲ አረቢያ የኢትዮጵያው አምባሳደር እና አንዳንድ ዲፕሎማቶች ሳውዲ አረቢያ የተመደቡበትን መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ከተለያዩ አሰሪ እና ሰራተኛ አገናኝ ኤጀንሲ ባለቤቶች ጋር በመመሳጠር በዜጎቻችን የህይወት ንግድ ላይ የተሰማሩ መሆናቸውን ይዘረዝራሉ። ምንም አይነት ቅድመ ዝግጀት ሳይደረግ በተለያዩ ግዜያት በቤት ሰራተኝነት ወደ ሳውዲ አረቢያ ህጋዊ በሆነ መንገድ የሚገቡ ወገኖቻችን ላይ በአሰሪዎቻቸው የወር ደሞዛቸውን ተነጥቀው ለህይወታቸ አደገኛ የሆነ የአካል ጉዳት እና በደል ተፈጽሞባቸው ብሶታቸውን ለመግለጽ ወደ ኤምባሲ የሚመጡ ተበዳዩችን የተጠቀሱት ዲፕሎማቶች አሰሪ እና ሰራተኛ አገናኝ፡ኤጀንሲዎችን ከተጠያቂነት ለማዳን የተበዳዮችን ጉዳዩ በማቅለል እና በማድበስበስ እህቶቻችን ለተጨማሪ ስቃይ በደል እና ግፍ በመዳረግ በሰው ሃገር የትም ወድቀው እንዲቀሩ ምክንያት መሆናቸው ይነገራል።

በተለይ በሪያድ የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ ማህበር ሊቀምንበር አቶ ሙስጠፋ ሁሴን ስም ኤጀንሲ ከፍተው በህጋዊ «ነገር ግን በመንግስት በኩል ምንም ቅድመ ዝግጀት በሌለው» የሰው ንግድ ስራ ላይ እንደተሰማሩ የሚታሙት ክቡር አምባሳደር መሃመድ ሃሰን ወደ ሃገር በአስቸኳይ መጠራታቸው ጉዳዩ ከሰሞነኛው ተቃውሞ ጋር የተያያዘ መሆኑንን የሪያድ እና አካቢው ነዋሪዎች የገልጻሉ። ዛሬ ማምሻውን ወደ ኢትዮጵያ እንደሚያቀኑ የሚነገርላቸው አምባሳደር መሃመድ ሃሰን አብዛኛው የሪያድ ህዝብ በአይን አይቶ እንደማያውቃቸው እና የአንባሳደሩ የቢሮ በር የሚከፈተው በገንዘብ ለጠረቁ ጥቂት ሃብታሞች እና በዜጎቻችን ህይወት የአየር በአየር ንግድ ለተሰማሩ የአሰሪ እና ሰራተኛ አገናኝ ኤጀንሲ ባለቤቶች ብቻ እንደ ሆነ ተበዳዮቹ ያወጋሉ።

ይህ በዚህ እንዳለ በተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞች እርስ በእርሳቸው እንደማይስማሙ እና በአይነቁራኛ እንደሚተያዩ የሚነግርላቸው በሪያድ የኢትዮጵያ ዲፕሎማቶች ህዝብ እና መግስት ከጣሉባቸው ሃላፊነት ውጭ፡ በተናጥል በሚወስዱት እርምጃ በኮሚኒቲው ንብረት ላይ አያሌ ጉዳቶችን አድርሰዋል። ከዚህ ባሻገር በኢትዮጵያ መንግስት ዘንድ በስፋት እየተነገረለት ባለው በታላቁ የአባይ ግድብ ቦንድ ሽያጭ፡ ሽፋን ጉዳዮቻቸውን ለማስፈጸም ወደ ኤንባሲው ከሚመጡ ወገኖቻችን ላይ በሃይል ያለ ገንዘብ መቀበያ ደረሰኝ ከእያንዳንዱ ሰው በነፍስ ወከፍ ከስከ 350 ሪያል ( ሁለት ሺህ አምስት መቶ ብር ) የሚደርስ ገንዘብ ህገወጥ፡በሆነ መገድ በመሰብሰብ የህዳሴውን ግድብ ታላቅነት ከማርከሳቸውም በላይ ዲፕሎማቱ እየፈጸሙ ባለው ስህተት ህዝብ እና መግስትን አራርቀዋል።

በክቡር አንባሳደር መሃመድ ሃሰን የሚመሩት እነዚህ የሪያድ ዲፕሎማቶች ለሰባዊ ክብሬ የሚቆረቋርልኝ አጋር አለኝ ብለው በአሰሪዎቻቸው ተደፍረው አሊያም ገነዘባቸውን ተነጥቀው እና የአካል ጉዳት ደርሶባቸው ወደ ሪያድ የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ ቅጥር ግቢ የሚያቀኑ እህቶችን ወደ ግቢው እንዳይገቡ በማገድ በዜጎቻን ህይወት ላይ ከመፍረድ የማይመለሱ ወገናዊ ረህራሄ የማይታይባቸው መሆናቸው ይነገራል፤፡ በአንጻሩ «ከመሞት መሰንበትን» መርጠው ከነዚህ የሪያድ ዲፕሎማቶች ጋር በማንኛውም ጉዳይ ተደራድረው እጅ መንሻ ቤጤ በመፈጸም ወደ ተጠቀሰው ግቢ የመግባት እድል የገጠማቸው ዜጎቻችንን አነስተኛ በሆነች ጌዜያዊ የኮንቴነር መጠለያ ተብሎ በሚነገርላት የምድር ሲኦል ውስጥ በማጎር ከየተኛውም ማህበረሰብ ጋር እንዳይገናኙ በር ተከርችሞባቸው ቀጣይ ህይወታቸውን በመጠባበቅ በሳውዲ አረቢያ የአየር ግለት በአሰቃቂ ሁኔታ እየነፈሩ እራሳቸውን የሚስቱ ወገኖቻችን ማየት የተለመደ መምጣቱን አንዳንድ ታዛቢዎች ይጠቅሳሉ ። እነዚህ ግፍ እና መከራ በሳዲ አረቢያ እንዲቀበሉ እየተገደዱ ያሉ ንጹሃን ወገኖቻችን ዛሬ ከስቃይ የታደጉ እየመሰላቸው መታነቅ አሊያም መርዝጠጥቶ ውድ ህይወታቸውን ማጥፋት አማርጭ የሌለው መፍትሄ ብለው ተያይዘውታል።

ይህን ሁሉ እውነታ በቅርቡ ሪያድን ጎብኝተው የተመለሱት በወጭ፡ጉዳይ ሚኒስቴር መ/ቤት የመንግስት መለዕክተኛ ዶ/ር ደስታ ወ/ዮሃንስ በምስል መቅረጫዎቻቸው እውነታዎችን ለኤግዝቢትነት መዝግበዋል ፤ በሪያድ የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ ጊዚያዊ መጠለያ የሚኖሩ የሴት እህቶቻችንንም ስቃይ እንባ እየተናነቃቸው ጎብኝተዋል ፤ ከዚህም በላይ ወይዘሮዋ በዚህ እና መሰል ተዛማጅ ጉዳዩች የአካባቢውን ነዋሪ በተናጥል እና በጋራ በግልጽ አነጋግረዋል ፤ አምባሳደር መሃመድ ሃሰን ለውጭ ጉዳይ ሚኔስቴር መ/ቤት ለመላክ አሻፈረኝ ያሉትን በሳውዲ አረቢያ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን ብሶት ያዘለች ባለ 5 ገጽ ደብዳቤ ከአካባቢው የሃገር ሽማግሌዎች እና ተዋቂ ግለሰቦች ተቀብለው ለመንግስት ለማድረስ ወደ መጡበት አቅንተዋል።
ዛሬ በሪያድ የኢትዮጵያው አምባሳደር መሃመድ ሃሰን በአስቸኳይ ወደ ኢትዮጵያ መጠራታቸው ማለፊያ ቢሆንም ሰሞኑን መንግስት በተለያዩ ድህረ ገጾች እና በውጭ፡ጉዳይ መ/ቤት የሴቶች እና የህጻናት ጉዳይ ተጠሪ አማካኝነት በአይኑ ሲያይ ለከረመው አስፋሪ ክስተት አፋጣኝ የሆነ ዘላቂ መፍትሄ ሊያፈላልግለት እንደሚገባ በሳውዲ አረቢያ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ወገኖች ብቻ ሳይሆነ ! ለሃገር እና ለወገን ተቆርቋሪ የሆኑ ኢትዮጵያዊያን ሁሉ ጥያቄ ነው ።

ዘግይቶ የደርሰ ዜና የሪያድ እና አካባቢው ኢትዮጵያውያን ነዋሪዎች ሰሞኑንን አምባሳደር መሃመድ ሃሰን እና በሪያድ የኢትዮጵያ ዲፕሎማቶቹ ላይ ባሰሙት ተቃውሞ የምስክርነት ቃላቸውን ለመስጠት ተወካዮቻቸውን እንዲልኩ ከኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚ/መ/ቤት በቀረበላቸው ጥያቄ መሰረት ከህዝብ የተመረጠ 3 አባላት ያለው ቡድን ትላንት ማምሻውን አምባሳደሩን ተከትሎ ወደ ኢትዮጵያ ማቅናቱን ከሪያድ የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ ማዕከል አካባቢ የሚወጡ ሚስጥራዊ መረጃዎች አረጋግጠዋል ።

ከ Ethiopian Hagere ( ሳውዲ አረቢያ ጅዳ በዋዲ )

No comments:

Post a Comment