ክፍል አንድ
አጽዋማት፡- ጾም ለተወሰነ ሰዓት ከሁሉም ምግብ መከልከል ሁሉንም ምግብ መተው ነው፣ ለተወሰኑ ቀናት ማለት የጾሙ ቀናት እስኪያልፍ ድረስ ከተወሰኑ ምግቦች መከልከል የተወሰኑ ምግቦችን መተው ነው፣ ይኸውም ጥሉላትን ፈጽሞ መተው ሰውነትን ከመብልና ከመጠጥ መከልከል መጠበቅ ነው፡፡ ጾም ከጥሉላት መከልከል ብቻ ሳይሆን የሰው ልጆችን ከሚጐዳ ነገር ሁሉ መከልከልንና ለሌሎች መልካም ሥራ መሥራትንም ይጨምራል፡፡
በማንኛውም የሃይማኖት ሥርዓት ጾም አለ፤ የአፈጻጸሙ ሥርዓት ግን የተለያየ ሁኖ ይታያል፤ ለምሳሌ ያህልም ዕብራውያን ሲጾሙ ውለው ማታ ጥሉላት ይመገባሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ የክርስትናው እምነት ተከታይ እንደእኛይቱ ቤተ ክርስቲያን ሲጾሙ ውለው ሰዓት ሲደርስ እህልና ውሃ ብቻ ይቀምሳሉ እንጂ የጾሙ ወር ወይም ሳምንት እስኪፈጸም ድረስ ጥሉላት ፈጽሞ ክልክል ነው፤ የአጽዋማት ሥርዓት ሲባል ጾም እንዴት እንደሚገባና እንዴት እንደሚወጣ፣ እንዴትና ለምን እንደሚጾም ለይቶ ማወቅና እንደ ሥርዓቱ መፈጸምን የሚያመለክት ነው፤ የጾምን አላማና ጥቅም በሚመለከት የሸዋ ሊቀ ጳጳስ የነበሩት ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ "የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ" በሚለው መጽሐፋቸው "የበዓላትና የአጽዋማት ቀኖና" በሚል ርእስ እንደሚከተለው ገልጠውታል፡፡ "ጾም /ጦም/ ማለት ሰውነት ከሚፈልጋቸው ነገሮች ሁሉ መከልከል መወሰን ማለት ነው፡፡ ወይም ለሰውነት የሚያምረውንና የሚያስጐመዥውን ነገር መተው ማለት ነው፡፡ ጾም ከሃይማኖት ጋር ዘለዓለማዊ ዝምድና ስላለው ሃይማኖት ባለበት ቦታ ሁሉ ጾም አለ፡፡ ይልቁንም በብሉይ ኪዳን ጾም ከፍተኛ ቦታ አለው፡፡ የብሉይ ኪዳን ነቢያት ከእግዚአብሔር ጋር በሚገናኙበት ወራት እህልና ውሃ በአፋቸው አይገባም ነበር፡፡ /ዘፀ፡34፡28/ በኀጢአት ብዛት የታዘዘው የእግዚአብሔር መዓት የሚመለሰው ሕዝቡ በጾም ሲለምኑትና ሲማልዱት ነበር፡፡ /ዮናስ 2፣7-10/ "በሐዲስ ኪዳንም ጾም ሰው ሠራሽ ሕግ ሳይሆን ራሱ መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሥራ መጀመሪያ አድርጎ የሠራው ሕግ ነው፡፡(ማቴ 4፣2፤ ሉቃ.4፣2) ይህም ብቻ ሳይሆን በቁራኝነት አብሮ የሚኖር መንፈስ ርኩስ ሰይጣን እንኳ በጾም የሚወገድ መሆኑን መድኀኒታችን ተናግሮአል፡፡ (ማቴ.17፣21፤ ማር.9፣2) ቤተ ክርስቲያንን እንዲያገለግሉ የታዘዙ ሐዋርያትም በየጊዜው ከመንፈስ ቅዱስ ትእዛዝ የሚቀበሉት በጾምና በጸሎት ላይ እንዳሉ ነበር፡፡ (የሐ.ሥራ 13፣2) ለስብከተ ወንጌል የሚያገለግሉ ዲያቆናትና ቀሳውስትም የሚሾሙት በጾምና በጸሎት ነበር፡፡ (የሐ.ሥራ 13፣3፤ 4፣23፤) እነቆርኔሌዎስ ያላሰቡትን ያዩና ያገኙ በጾምና በጸሎት ፈጣሪያቸውን ማልደው ነው፡፡ (የሐ.ሥራ 10፣30) "የጾም ሃይማኖታዊ ትርጒም ፈጣሪን መለመኛ ከኀጢአት ቊራኛ መላቀቂያ መሣሪያ ስለሆነ በጾም ወራት ላምሮት ለቅንጦት የሚበሉ ወይም ለመንፈሳዊ ኀይል ተቃራኒ የሆነ ሥጋዊ ፍትወትን የሚያበረታቱ የአልኮል መጠጦችን፣ ሥጋንና ቅቤን፣ ወተትንና እንቁላልን ማራቅ ታዟል፡፡ ከመባልዕትና ከሌላው ደስታ ሁሉ ጋር ባልና ሚስት በምንጣፍ በአልጋ አይገናኙም፡፡ (1ቆሮ.7፣5) ጾም በትምህርተ ሐዋርያትና በሊቃውንትም ዘንድ ሲሰበክ ኑሯል፡፡ ነዳያንን ለመመገብ የሚጾም ንዑድ ነው፤ ክቡር ነው፡፡ እንደተባለ ጦመኛው ለምሳው ወይም ለራቱ ያለውን ወጭ ነዳያን እንዲረዱበት ለድኩማን መርጃ ድርጅት ወይም በቤተ ክርስቲያን አካባቢ ለሚገኙ ነዳያን መስጠት ጾሙን የበለጠ ክርስቲያናዊ ያደርገዋል፡፡ "ጾም የታሪክ ድርጊቶችን እያስታወሱ ከኀጢአት ለመንጻት ስለራሱ የታሰበውን ለነዳያን በመስጠት የሚጾም መሆኑን ተረድተናል፡፡ ጾም ለራስ ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም፤ ለወዳጅ ብቻ ሳይሆን ለጠላትም ይጾማል፤ ‹ለሚያሳድዱህ ጹምላቸው› እንደተባለ (ዲድ፡1፣3፤) በደዌ ዳኛ በአልጋ ቊራኛ የተያዙትን፣ በምርኮና በስደት ያሉትንም በጾም ወራት ማስታወስና መጸለይ ይገባል፡፡ በጾም ወራት ከመባልዕት መከልከል ብቻ ሳይሆን ዐይን ክፉ ከማየት፣ አንደበት ክፉ ከመናገር፣ ጆሮ ክፉ ከመስማት መቆጠብ እንደሚገባ ተጽፎአል፡፡ "ይጹም ዐይን፣ ይጹም ልሳን፣ እዝንኒ ይጹም እምሰሚዐ ኀሡም በተፋቅሮ" (ቅዱስ ያሬድ ድጓ) በሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን ባህልና ትውፊት ውስጥ ያሉ የምዕራብም ሆኑ የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት ከሐዋርያት የወረሱት የጾም ሕግና ሥርዐት አላቸው፡፡ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንም ከመጀመሪያዎቹ አብያተ ክርስቲያናት አንድዋ ስለሆነች ይህ የጾም ሕግና ሥርዓት አላት፡፡ በሕጓም መሠረት ሰባት የጾም ወራት አሏት፡፡ እነርሱም፡-
1. ዐቢይ ጾም፣
2. ጾመ ሐዋርያት፣
3. ጾመ ፍልሰታ፣
4. ጾመ ነቢያት፣
5. ጾመ ገሃድ፣
6. ጾመ ነነዌ፣
7. ጾመ ድህነት ናቸው፡፡
No comments:
Post a Comment