Thursday, August 22, 2013

ጉዞ ወደ ምድር ጥግ (ክፍል አራት) በዳንኤል ክብረት


ባለፈው ሳምንት በቡሩኖ ደሴት በምትገኘው ብሩናይ አውሮፕላን ማረፊያ ነበር የተለያየነው፡፡ አንዲት የሀገሬን ሰዎች የመሰለች ልጅ ወደ እኔ አቅጣጫ ስትመጣ አይቼ፡፡ ልጅቱ መጣች፡፡ እንደ ዓይኔ ምስክርነት ከሆነ የሀገሬ ልጅ ናት፡፡ በአንገቷ ላይ ጣል ያደረገችው ሻርፕ ነገርም ነጠላ ቢጤ ነው፡፡ እንዲያውም የሆነ ጥልፍ ነገር ይታየኛል፡፡ መጣችና ከእኔ በትይዩ ከሚገኘው የተደረደረ ወንበር መካከል ተቀመጠች፡፡ ይኼኔ ዓይኔን ተጠራጠርኩት፡፡ ኢትዮጵያዊት አይደለችም ማለት ነው? አልኩ በልቤ፡፡ መሆን አለመሆኗን ለማረጋገገጥ የሆነ ምልክት መፈለግ ጀመርኩ፡፡ ምንም ነገር ሳጣ ‹‹ለምን አልጠይቃትም›› አልኩና አመራሁ፡፡
ወደ ወንበሯ ስጠጋ ባደረገችው ሻርፕ ላይ ኦዳ (የኦሮሞ ባሕላዊ መለያ የሆነው ዋርካ) ተጠልፎ አየሁት፡፡ በዚህ ተጽናናሁና
‹‹ኢትዮጵያዊት ነሽ›› አልኳት በአማርኛ፡፡
‹‹ይቅርታ አይደለሁም›› አለችኝ በእንግሊዝኛ፡፡
‹‹ይህንን የልብሱን ጌጥ ግን ዐውቀዋለሁ›› አልኳት እኔም በእንግልጣር፡፡
ቀና ብላ በአግራሞት እያየችኝ ‹‹ልክ ነህ ኦዳ ነው›› አለችኝ፡፡
‹‹ታድያ ቢያንስ በትውልድ ኢትዮጵያዊ ነሻ›› አልኳት እንደ ቀልድ፡፡
‹‹አይደለሁም›› ብላኝ ኮስተር አለች፡፡
እንዲህ ዓይነት ነገር በአሜሪካ ሚነሶታ አጋጥሞኝ ስለሚያውቅ ተጠራጠርኩና በእንግሊዝኛ ‹‹ይቅርታና ታድያ የየት ሀገር ሰው ነሽ?›› አልኳት፡፡
 
አሁን ከእርሷ አለፍ ብየ ቁጭ ብያለሁ፡፡ ‹‹እኔ ከኦሮሚያ ነኝ›› አለችኝ፡፡ ስልኳን እየነካካች፡፡
‹‹እኔምኮ ከኦሮሚያ ነኝ፡፡ አዲስ አበባ የኦሮሚያ ዋና ከተማ አይደለች እንዴ›› አልኩ ለቀልድ ያህል፡፡
‹‹አዲስ አበባ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ ናት፤ የኦሮሚያ ዋና ከተማ ፊንፊኔ ናት፡፡ አሁን እኔና አንተ መነጋገሩ ምን ይፈይድልናል›› አለች ለመገላገል ብላ፡፡
‹‹እኔና አንቺ ካልተነጋገርንማ ማንና ማን ተነጋግሮ መፍትሔ ያመጣል ታድያ››
‹‹ምናልባት ላንግባባ ስለምንችል››
‹‹አለመግባባታችንን በምን ዐወቅሽው?››
ተመቻቸችና ‹‹ለምሳሌ እኔ ፊንፊኔ ስል አንተ አዲስ አበባ አልክ፣ ለእኔ ኦሮሚያ ቅኝ የሚገዛ ሀገር ነው፤ ላንተ ደግሞ ክልል ነው፤ ታድያ እንዴት እንግባባለን?››
‹‹ሰዎች ሊግባቡ የማይችሉትኮ የተለያዩ ሃሳቦችን ስለሚይዙ አይደለም፡፡ የተለያዩ ሃሳቦቻቸውን የማስማሚያ መንገድ ስለማይኖራቸው ነው፡፡ ደግሞም የግድኮ መግባባት አይጠበቅብንም፤ ቢያንስ እንገናዘባለን፡፡ አሁን አንቺ ፊንፊኔ አልሽ፣ እኔ አዲስ አበባ አልኩ፤ ምናልባትም ከአዲስ አበባና ከፊንፊኔ በፊትም ቦታው ሌላ ስም ሊኖረው ይችላል፡፡ አዲስ አበባ ከየቦታው በግድም በውድም የመጣን የሀገሬው ሰዎች ብቻ ሳንሆን ጣልያኖችም፣ ግሪኮችም፣ ዐረቦችም፣ አርመኖችም፣ እንግሊዞችም፣ ፈረንሳዮችም፣ ሌሎችም ባዋጣነው አስተዋጽዖ እዚህ ደርሳለች፡፡ እንዲያውም በሌላው ሀገር እንዲህ የብዙ ዓይነት ወገን አሻራ ያረፈባት ከተማ ስትገኝ እንደ ልዩ ነው የምትታየው፡፡ የሚፈለገውም የሁሉ እንድትሆንና ሁሉም አስተዋጽዖውን የእኔ ብሎ እንዲቀጥል ነው፡፡ ቻይና ታውን፣ ኢትዮጵያን ስትሪት፣ ኮርያ ሠፈር፣ ስፓኒሽ ጎዳና እያሉ ለአስተዋጽዖ አድራጊዎቹ ዕውቅና በመስጠት የሁሉ እንድትሆን ያደርጓታል፡፡ አዲስ አበባ ወይም ፊንፊኔም እንዲሁ ናት፡፡
‹‹በሕዝብ ፍልሰትና በጦርነት በኖረ ሀገር የስም ተፋልሶ ያለ ነገር ነው፡፡ ለምሳሌ በምዕራብ ሸዋ ‹ወረብ›ና ‹እንደገብጦን› የሚባሉ የጋፋቶች ግዛቶች ነበሩ፤ በኋላ ግን በኦሮምኛ ስሞች ተተክተዋል፡፡ በምሥራቅ ሸዋ እነ ፈጠጋር፣ እነ ወጅ፣ እነ መሐግል ስማቸውን አጥተው ቀርተዋል፡፡ ዛሬ የመተሐራ አካባ የሚባለው ጥንት መሐግል ነበረ፡፡ ጎጃም ብትሄጂ አቸፈር፣ ሜጫ፣ አዴት፣ ዴንሳ፣ ብቸና የኦሮሞኛና የኦሮሞኛ ነክ ስሞች ናቸው፡፡ በፊት ግን የአገውና የአማራ ስሞች ነበሩባቸው፡፡ ያ ማለት ግን ቅኝ ተገዝተዋል ማለት አይመስለኝም፡፡
‹‹በባሌ፣ በሐርና በሸዋ ብዙ የአርጎባ ስሞች ወደ ኦሮምኛ ተቀይረዋል፡፡ በወለጋና በደቡብ ሸዋ ሰባቱ የጋፋት ፌዴሬሽን አካላት ይገኙባቸው የነበሩ ቦታች ዛሬ ሰዎቹም ስማቸውም ጠፍቶ ቀርቷል፡፡ ስማቸው ብቻ አይደለም፡፡ በኢትዮጵያ የጥበበ ዕድ ኢንዱስትሪ ታላቅ ቦታ የነበራቸው፣ በሕክምናና አስተዳደር ችሎታቸው የተመሰከረላቸው ጋፋቶች በኦሮሞ ፍልሰት ጊዜ ከመካከልና ከደቡብ የሀገራችን ክፍሎች ወጥተው መጀመሪያ ወደ ጎጃም ተሻገሩ፤ ከዚያም ደግሞ ቀስ በቀስ እየተዋጡ ጠፉ፡፡ ዛሬ ቋንቋቸውም ሆነ ባህላቸው ከኦሮሞዎች፣ ከአማሮችና ከአገዎች ጋር ተዋሕዶ ሕልውናውን አጥቷል፡፡
‹‹በትግራይ፣ በወሎና በጎጃም የአገው ሕዝቦች ከጥንት ጀምሮ ተስፋፍተውባቸው የነበሩ ቦታዎች በአማራና በትግራይ ሕዝብ ተውጠው፣ ስማቸውንም ቀይረው ጠፍተዋል፡፡ በደቡብ ምዕራብ ትግራይ የነበሩት የዶባ ሕዝቦች በአፋርና በትግራይ ተውጠው የቦታዎቻቸው ስሞችም ተቀይረው፣ ከጥቂቶች በቀር ጠፍተዋል፡፡ የጥንቷ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ተብለው የተመዘገቡትኮ አሁን ስማቸውን እንኳን አንሰማውም፡፡ ምናልባት ከአገው ሕዝቦች በቀር፡፡ ክርስቲያን ቶፖግራፊ በተሰኘው የኮስሞስ መጽሐፍ ውስጥ በአዱሊስ ያገኘውን የካሌብ የድንጋይ ጽሑፍ አኑሮልናል፡፡ በዚያን ጊዜዋ ኢትዮጵያ የተገለጡት ሕዝቦች ጋዜ፣ አጋሜ፣ ሲጊን፣ አቫ፣ ዚጋሪን፣ አጋቬ፣ ቲያማ፣ አታጋውስ(አገዎች)፣ ካላ፣ ሰሜን፣ ላዚን፣ ዚአ፣ ጋቫላ፣ አታልሞ፣ ቤጃ፣ ›› የሚባሉ ሕዝቦች ናቸው፡፡ ብዙዎቻችን እዚህ ዝርዝር ውስጥ የለንም፡፡ እነዚህ ቦታዎች ግን ዛሬ ወይ የወንዝ፣ ወይ የጎጥ፣ ወይ የተራራ ስሞች ሆነው ቀርተዋል፤ ያለበለዚያም ተለውጠዋል፡፡ ወሎ ብትሄጂ የአማራው ዋና ቦታ የነበረው ወለቃ ዛሬ ስሙ ቦረና ተብሏል፡፡ ወለቃ የወንዙ ስም ሆኖ ቀርቷል፡፡›› ስልኳን እየነካካችም ቢሆን ስትሰማኝ ቆየችና
‹‹የኦሮሞ ሕዝብ ግን የተለየ ነው፤ የሀገሪቱን ሰፊ ክፍል ይዞ ከሀገሪቱ ተጠቃሚ ሳይሆን፤ መሬቱንና መብቱን ተቀምቶ በገዛ መሬቱ ለሌሎች ገባር ሆኖ፤ ቋንቋውና ባህሉ ተረግጦ፤ ሌሎች ሕዝቦች መጥተው አገሩን ወስደውበት የሚኖር ሕዝብ ነው፡፡ በግድኮ ነው ኢትዮጵያ የሆነው፤ ኢትዮጵያ የሰሜን ሕዘቦች እንጂ የደቡቦቹ መጠሪያ አይደለችም፡፡ ኢትዮጵያ ሌላውን ጠቅልላ ነው የያዘችው፡፡›› አለችኝ፡፡ መነጋገሩን ወዳዋለች ማለት ነው፡፡
‹‹እይውልሽ እኅቴ እኔኮ በኦሮሞ ሕዝብ ላይ ምንም ነገር አልደረሰም፤ መብቱ አልተነካም፣ መከራ አልተቀበለም፤ አልተሰቃየም፤ መሬቱን አልተነጠቀም፤ ሌሎች መሬቱን አልወሰዱበትም አይደለም የምልሽ፤ ነገር ግን ይህ ነገር የብዛትና ማነስ ካልሆነ በቀር በሁሉም ላይ የመጣ ነው፡፡ በዚያች ሀገር ውስጥ ለሥልጣንና ለሀብት ብዙ ትግግሎች ተደርገዋል፡፡ ‹‹ወረራ››፣ ፍልሰት፣ ጦርነት፣ ንጥቂያ፣ ስደት ተከስቷል፡፡ ይህ ግን የአንድ ሕዝብ ብቻ ስቃይ መገለጫ አይደለም፡፡ የብዛትና ማነስ ካልሆነ የሁላችንም አያቶች ቀምሰውታል፡፡ ጎንደሬው ዐፄ ቴዎድሮስኮ ጎንደሬዎቹን እጃቸውን ቆርጠዋል፣ በአንድ ቤት ውስጥ አስገብተው አቃጥለዋቸዋል፡፡ እንዲያውም ኦሮሞውን ምንም አላደረጉትም፡፡ ያ ግን የሥልጣን ጥያቄ እንጂ በአንድ ዘር ላይ የተፈጸመ ወንጀል አይደለም፡፡ ሁላችንም የያዝነው የተፈጠርንበትን መሬት ብቻ አይደለምኮ፡፡ ኦሮሞውም ቢሆን ከአማራው፣ ከትግሬው፣ ከጋፋቱ፣ ከአርጎባው፣ ከጉራጌው፣ ከሲዳማው፣ ከሌሎች ከጠፉ ሕዝቦች መሬት ወስዷል፡፡ ሁላችንም እዚህ አይደለም የነበርነው፤ አስፍተን ይዘናል፤ ተገፍተን ለቅቀናል፤ ተውጠን ቀርተናል፤ ውጠን ተዋሕደናል፡፡ የነገሥታቱን ታሪክ ስናይኮ የኦሮሞውም ሕዝብ ወደ ሸዋ፣ ወደ ጎጃም፣ ወደ ጎንደርም እየዘለቀ ከብት ዘርፏል፤ ሰዎች ገድሏል፤ እህል አቃጥሏል፡፡ መሬት ወስዷል፡፡ በጎጃምና በወለጋ ኦሮሞዎች ዘንድ ዓባይን እያለፉ የመዘራረፍ፣ የመገዳደል፣ የመዋጋት፣ ከዚያም በላይ የመጋባት ታሪክ ነበርኮ፡፡ ይህኮ ለኢትዮጵያ አዲስ አይደለም፡፡ ሁላችን እንዲህ ሆነን ነው እየተፈጠርን የመጣነው፡፡ ደግሞም ‹የመርገምት በረከት› እንደሚባለው ይህ ነገር አዋሕዶ ፈጥሮናል፡፡
‹‹የነበረው ትግልኮ ሀብትና ሥልጣንን መሠረት ያደረገ እንደነበር የምታዪው አንድ ‹ዘር› የሚባሉትም እርስ በርሳቸው ሀብትንና ሥልጣንን ለመንጠቅ ሲሉ ሲዋጉ መኖራቸው ነው፡፡ ዐፄ ቴዎድሮስ ጎጃም ገብተው ብዙ ሕዝብ ጨርሰዋል፡፡ ሞጣ አካባቢ ብትሄጂ የሚዘገንን ታሪክ ይነግሩሻል፡፡ ሸዋ ወርደው ብዙ እጆች ቆርጠዋል፡፡
ዐፄ ቴዎድሮስ እጅግ ተዋረዱ
የሸዋን ሰው ሁሉ እጅ ነሥተው ሄዱ የተባለውን አልሰማሽ፡፡
ያንን ግን አማራውን ከመጨቆንና ከማጥፋት አንጻር ካየነው፣ ቅኝ ግዛት አድርገን ከተመለከትነው ስሕተት ይመስለኛል፡፡ ሰዎች ተጨቁነዋል፤ አዎ፡፡ በራስ ሚካኤል ጊዜ ወሎና ሸዋ ተዋግቷል፡፡ በምኒሊክና በተክለ ሃይማኖት ምክንያት እምባቦ ላይ ሸዋና ጎጃም ተጫርሷል፡፡ ዐፄ ሱስንዮስ ከሸዋ አስከትለዋቸው ለሄዱት የኦሮሞ ወታደሮች የጎንደርን መሬት ከየአድባራቱ እየቀሙ እንዳደሏቸው የማኅደረ ማርያም ታሪክ በዝርዝር ይነግረናል፡፡ አንዱ ከካህናቱ ጋር ያጣላቸውም ይኼው ነበር፡፡
ዐፄ ታዎፍሎስ (1701-11) በነገሡ በሦስተኛው ዓመት ኦሮሞዎች ወሎ አምሐራ ሳይንት ወደምትገኘው አትሮንሰ ማርያም ደብር ገብተው በሮቿን ሰበሩ፤ ካህናቱንም በሙሉ ገደሉ፡፡ ምእመናኑንም ሁሉ ማረኩ፤ ዐፄ በዕደ ማርያም በፈረንጅ እጅ ያሳለውን የእመቤታችንን ሥዕልና የዐፄ በዕደ ማርያምን ዐፅም ሁሉ ነሐሴ 9 ቀን አውጥተው መሬት ለይ ጣሉት›› ይላል ዜና መዋዕሉ፡፡ እንግዲህ ይህንን ስታዪ እዚህች ሀገር ሳያጠፋም ሳይጠፋም የኖረ ሕዝብ አለመኖሩን ነው የምታዪው፡፡ ይህ ግን ኦሮሞዎች የኦርቶዶክስን እምነት ለማጥፋት፣ ወይም አማሮችን ለማጥፋት ብለው ያደረጉት አይመስለኝም፡፡ የሀብትና የሥልጣን ትግል ነው፡፡
ደግሞም በአንድ አካባቢ በነበረ ስም ተጠቅልሎ መጠራት በኛ አልተጀመረምኮ፡፡ ሀገር ተቀናንሶ ያንሳል፤ ወይም እምብርቱን ይዞ እየሰፋ ይሄዳል፡፡ አፍሪካ የሚለው ስም ላቲኖች በዛሬዋ ቱኒዚያ ለነበሩት ካርታጎአውያን የሰጡት ስም ነበረ፡፡ በመጀመሪያ አካባቢ የሊቢያ ጎሳዎችን ለመጥራት ነበር የሚውለው፤ በበርበሮች ቋንቋ ‹ኢፍሪ; ማለት ‹ዋሻ› ማለት ሲሆን ‹‹በዋሻ የሚኖሩ›› ለማለት የተጠቀሙበት ነው፡፡ ላቲኖች ‹ኢፍሪ› በሚለው ላይ ‹ኢካ› የሚለውን ለቦታ የሚቀጠል ቅጥያ ቀጠሉበትና ‹አፍሪካ› ብለው ጠሩት፡፡ በኋላ ግን የሁላችንም መጠሪያ ሆነ፡፡ እስያ ጥንት ዛሬ ቱርክ የያዘችው ቦታ መጠርያ ነበር፡፡ ዛሬ ግን እንዲያውም የሚጠሩበት የሩቅ ምሥራቅ ሕዝቦች ናቸው፡፡
‹‹አየህ›› አለችኝ መነጽሯን አስተካክላ፡፡ ‹‹አየህ አንተ ጭቆናው አይሰማህም፤ ምክንያቱም ከተጨቆኑት ወገን አይደለህምና፡፡ የደረሰብህ ነገር የለም፤ የመከራውን ገፈት አልቀመስከውም፡፡ እንደኛ በገዛ ሀገርህና መሬትህ ግፍ ቢደርስብህ፣ እንደኛ ቅኝ ተገዝተህ የቅኝ ግዛትን መራራ ነገር ብትቀምሰው እንደዚህ አትልም ነበር፡፡ አንዱ ልዩነታችን ከዚህ የሚመጣ ነው፡፡ በተግባር በቀመሰውና በትምህርት በሚያውቀው መካከል የሚኖር ልዩነት››
‹‹አንቺምኮ ከሌሎች ሰማሽው፣ አነበብሽው ወይም ወረስሽው እንጂ አልደረሰብሽም፡፡ የደረሰና የሚደርስ ካለም በሁሉም ላይ ይደርስ ይሆናል እንጂ የተለየ ነገር አሁን አይደርስብሽም፡፡
‹‹ለምሳሌ በስድሳ ስድስት አብዮት ጊዜ በአብዛኛው በቀይ ሽብር ያለቁት ኦሮሞዎች ናቸው›› አለች ስልኩን ወንበሩ ላይ አስቀምጣ፡፡
‹‹በምን ታወቀ?››
‹‹መረጃዎች አሉ››
‹‹ማን ነው ያን ጊዜ ሬሳ እያገላበጠ ዘር እየቆጠረ መረጃ የሰበሰበው››
‹‹ቢያንስ አብዛኛው የሀገሪቱ ሕዝብ ኦሮሞ በመሆኑ በብዛት የሚሞተው እርሱ ነው››
‹‹እንዴ አንድ ሕዝብኮ በብዛት ይኖራል ማለት በብዛት ይሞታል ማለት አይደለም፡፡ በወቅቱ በነበረው ተሳትፎ ነው የሚወሰነው፡፡ ያኔኮ የመፈረጃው ሳጥን ፀረ አብዮት፣ ፀረ ሕዝብ፣ አድኃሪ፣ ቡርዡዋ፣ ኢሕአፓ፣ ምናምን የሚል ነው፡፡ የዘር ፍረጃ አልነበረውም፡፡ አንዳንዴ ችግሩ እኔ ብቻ ነኝ መከራ ያየሁትና እኔ ብቻ ነኝ መፍትሔ የሚያስፈልገኝ ከሚል የሚመጣም ይመስለኛል፡፡ ችግሮችን ለመፍታት መነሣት እንጂ የተወሰኑ አካላትን ከችግር ለማላቀቅ መነሣት ተመልሶ ባልተፈቱት ችግሮች ወጥመድ የሚጥል ነው፡፡››
‹‹ከሆነ አካባቢ ነገሥታቱ መነሣታቸው በዓለም ታሪክ የተለመደ ነው፡፡ እንደ ፓርላማ ሥርዓት ንጉሣዊ አስተዳደር ሁሉን ያማከለ ሊሆን አይችልም፡፡ ኖርዌይን ሲገዟት የኖሩት የዴንማርክ ንጉሣውያን ቤተሰቦች ናቸው፡፡ አሁንም በእንግሊዝ ንጉሣዊነት በዘር ግንድ የሚሄድ ነው፡፡ አሁንም በጃፓንና ስፔን እንዲሁ ነው፡፡ በእሥራኤልም ታሪክ ብናየው የይሁዳ ቤት ነው፡፡ ይኼኮ የሰው ልጅ በሆነ ዘመን የደረሰበት ደረጃ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከዚያ የተለየች አትሆንም፡፡
‹‹ነገሥታቱ ከአማራው ወገን ስለነበሩኮ በ66 አብዮት የአማራው ሕዝብ አጥር ሆኖ ከውድቀት አላዳናቸውም፡፡ ንጉሣዊው ሥርዓት ሲወድቅኮ በተማሪው ንቅናቄ፣ በወታደሩ፣ በፓርቲዎች፣ በሠራተኛ ማኅበሩ ውስጥ የተለያዩ ማኅበረሰቦች ናቸው የነበሩት፡፡ ጨቁነውናል ብለው ከተነሡት ሕዝቦች መካከልኮ አማሮችም፣ ትግሬዎችም፣ ኦሮሞዎችም፣ ሲዳማዎችም፣ ወላይታዎችም፣ ጉራጌዎችም፣ ሶማሌዎችም ነበሩበት፡፡ እንዲያ ባይሆን ኖሮማ ተጠቅመናል በሚሉት አማሮችና ተጨቁነናል በሚሉት ሌሎች መካከል የርስ በርስ ጦርነት ይነሣ ነበር፡፡ አሁንኮ ያለፈውን ታሪክ በግልጥ መነጋገር፣ ከዚያ ትምህርት መውሰድና እንዳይደገም ማድረግ ነው የሚሻለው፡፡ እኛ ስለ ትናንት ብቻ ስንከራከር፣ ስለ ነገም ሳንነጋገር ስንት መልካም አጋጣሚዎች በዚህች ሀገር አለፉ፡፡ ስለ ትናንት ታግለን አብዮት እናመጣለን፤ ለውጥ ሲመጣ ግን ለነገ ያዘጋጀነው የጋራ የመግባቢያ ሰነድ ስለሌለን እንደገና አዙሪት ውስጥ እንወድቃለን፡፡ ተባብረን መሸከም ያልቻልነውን ችግር ለየብቻ እንሸከመዋለን ብሎ መመኘት ቅዠት ነው የሚመስለኝ፡፡››
ደኅና ሞቅ ወዳለው ውይይት በመግባት ላይ ሳለን
‹‹ወደ ማኒላ የምትሄዱ መንገደኞች ወደ በሩ ግቡ›› የሚል ማስታወቂያ ተነገረ፡፡ ቦርሳዋን ሸክፋ ከመቀመጫዋ ተነሣች፡፡
‹‹ደስ የሚል ቆይታ ነበር፡፡ እኔ ወደ ፊሊፒን ነው የምሄደው፤ የምኖረውም እዚያ ነው፡፡ በፊት ደቡብ አፍሪካ ነበርኩ፡፡ አሁን ወደ ሰባት ዓመት ሆነኝ፡፡ እዚያ ከመጣህ እንገናኛለን›› አለችኝ፡፡ የኢሜይል አድራሻየን ሰጠኋት፡፡ ወደ በሩ ስትገባ ዘወር ብላ ሰላም አለችኝ፡፡ አንደበቷ እንጅ ነፍስያዋ የሀገሬ ልጅ መሆንዋን ይነግራታልኮ፡፡
እኔም ከጥቂት ደቂቃዎች ወደ አውሮፕላኔ ገባሁ፡፡ ወደ አውስትራልያ ለመድረስ የሰባት ሰዓት በረራ ይጠብቀኛል፡፡ በቸር ሜልበርን ላይ እንገናኝ፡፡
source: danielkibret.com

No comments:

Post a Comment